መከላከያ ሰራዊት ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መስራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል – ሌ/ጀ ሰለሞን ኢተፋ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መከላከያ ሰራዊት በሚያከናውናቸው የሰላም ማስፈንና ሌሎች ተግባራት ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሰለሞን ኢተፋ አስታወቁ።
የደቡብ ዕዝ 202ተኛ ኮር የ30ኛ ነበልባል ክፍለጦር ሶስተኛ ዓመት ምስረታ በዓል በአዋሽ ቢሾላ የስልጠና ማዕከል ዛሬ ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌ/ጀ ሰለሞን ኢተፋን ጨምሮ ሌሎች የዕዙ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም አባገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።
ሌ/ጀ ሰለሞን ኢተፋ በወቅቱ እንደተናገሩት ÷30ኛ ክፍለጦር በሚሰጠው ሀገራዊ ግዳጅ ጠንካራ የተልዕኮ አፈፃፀም ያለው መሆኑ የሚያኮራው ነው ብለዋል።
ክፍለጦሩ በአሁኑ ወቅት ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ገልፀው÷ሰራዊቱ በሚያከናውናቸው የሰላም ማስፈን ተግባራት ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በደቡብ ዕዝ የ202ተኛ ኮር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋዬ ÷ሰራዊቱ ሰላም በማስከበር በከፈለው መስዋእትነት የልማት ስራዎች እየተሳለጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የ30ኛ ክፍለጦር አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ለታ አንበሴ በበኩላቸው÷ ክፍለጦሩ የሀገሪቷን ዳር ድንበር በማስከበር ስመጥር መሆኑን አንስተው፤በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሰላም በማስከበር ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
በቀጣይም መከላከያ ሰራዊቱ በሚያደርገው የሰላም የማስከበር ስራ ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡