አይሲሲ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ላይ የእስር ማዘዣ ቆረጠ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እና በቀድሞ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ ቆረጠ።
ከእስራኤል ባለስልጣናት በተጨማሪ እስራኤል ባለፈው ሃምሌ ወር በጋዛ ላይ በፈጸመችው ጥቃት እንደተገደለ የሚታመነው የሃማስ ወታደራዊ አዛዥ መሐመድ ዴይፍ በፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣ የተቆረጠበት መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
የአይሲሲ ፍርድ ቤት ዳኞች እንዳስታወቁት፤ የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸውን ሰዎች በወንጀል ለመጠየቅ የሚያስችል መነሻ መሰረት አለ።
በእስራኤል ጋዛ ጦርነት ወቅት የጦር ወንጀል እና ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት እንዲፈጸም ስለማድረጋቸው የሚያመላክቱ ማስረጃዎች እንደቀረቡ ጠቁመዋል።
እስራኤልም ሆነች ሃማስ የጦር ወንጀል በመፈጸም የቀረበውን የእስር ማዘዣም ሆነ ውንጀላ የማይቀበሉት መሆኑን በመግለጽ አጣጥለውታል።