ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የገቢ እቃዎች ላይ የጥራት ቁጥጥር ተደርጓል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ 6 ወራት 1 ሚሊየን 719 ሺህ 973 ሜትሪክ ቶን የገቢ ምርቶች ላይ የጥራት ቁጥጥር ሥራ መከናወኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በስድስት ወራት በ1 ሚሊየን 888 ሺህ 926 ሜትሪክ ቶን የገቢ ምርቶች ላይ የኢንስፔክሸን ሥራ ለማከናወን መታቀዱን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ የዕቅዱን 91 ነጥብ 05 በመቶ ማሳካቱን አስታውቋል፡፡
በምርቶቹ ላይ የኢንስፔክሽን ሥራዎችን በማከናወንና በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት እንዲፈተሹ በማድረግ የኢትዮጵያን ደረጃ ያሟሉ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ፍቃድ መሰጠቱ ተገልጿል።
በተጨማሪም የውሃ ፓምፕ፣ የሶላር ቴክኖሎጂ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ ፍሪጅ፣ ጀነሬተር፣ ትራንስፎርመር፣ ኢንዳክሽን እና መሰል የገቢ ምርቶች ከሚመጡበት ሀገር ጥራታቸው ተረጋግጦ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እያቀረቡ እንዲስተናገዱ መደረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ ጠቁሟል፡፡
የጥራት ቁጥጥር ከተደረገባቸው አስገዳጅ ደረጃ የወጣላቸው ገቢ ምርቶች መካከል 932 ነጥብ 89 ሜትሪክ ቶን ምርቶች ከደረጃ በታች መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ ሀገር እንዳይገቡ መታገዱ ተገልጿል፡፡