ከተሰበሰበ ግብር 70 በመቶውን ህዝብን ለሚጠቅሙ ተግባራት አውለናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከህዝብ ከተሰበሰበው ግብር 70 በመቶው ህዝብን ለሚጠቅሙ ተግባራትና ለዘላቂ ልማት በማዋላችን የፈጣን ለዉጦቻችንን ቀጣይነት አስጠብቀናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የመንግስትና የፓርቲ ሥራ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡
ይህንን አስመልክተው ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፥ “ባለፉት ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸማችን ከተማችንን ከነዋሪዎቿ ኑሮ እና አኗኗር ጋር አስተሳስረን ውብ እና አበባ የማድረግ እንዲሁም የቱሪስት መተላለፊያ ሳትሆን መዳረሻ እንድትሆን ለማድረግ አቅደን እየሰራን ያለነውን ስራ ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ማድረግ እና ውጤታማነቱን ማስጠበቅ ችለናል “ብለዋል።
አስተዳደራዊ ወጪን እና ብክነትን በመቀነስ ከህዝብ ከተሰበሰበ ግብር 70 በመቶ የሚሆነው የነዋሪውን እንግልት ለሚቀንሱ፣ ህዝብን ለሚጠቅሙ ተግባራትና ለዘላቂ ልማት በመዋሉ የፈጣን ለውጦችን ቀጣይነት ማስጠበቅ መቻሉን አንስተዋል፡፡
አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የፀዳ ለማድረግ እና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አሰራርን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ታቅዶ የተሰሩ ስራዎችም ለውጦች ማሳየታቸውንም ነው ያነሱት።
የግምገማ መድረኩ ለቀጣይ ውጤታማነት መዘጋጃ እንደሚሆንም ከንቲባዋ ጨምረው ገልፀዋል፡፡