ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክቶች ላይ የተሻለ አፈፃፀም አሳይታለች – አቶ አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍራካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክቶች ላይ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገቧን የኢኒሼቲቩ ፕሮጀክቶች ሰብሳቢና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለፁ።
የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ቀጣናዊ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በጋራ ገምግመዋል።
የኢኒሼቲቩ ሰብሳቢና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ጉዳዩን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ፥ ኢኒሼቲቩ በቀጣናው ሀገራት የመሰረተ-ልማትና የሰው ሀብት ልማት፣ የግብርና፣ የጤና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሁም አደጋዎች መከላከል ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
እነዚህ የቀጣናው የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ ክትትል የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የቀጣናው የሰላምና የልማት ማዕከል በመሆኗ ኢኒሼቲቩ ውጤታማ እንዲሆን የማስተባበር ስራውን በትኩረት እየሰራች ትገኛለችም ነው ያሉት።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን በልማት ለማስተሳሰር የየሀገራቱ የገንዘብ ሚኒስትሮች ያቋቋሙት መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማት ካላት ፍላጎት አኳያ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን እየተገበረች መሆኑን ጠቅሰው ፥ እስካሁን ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ የልማት ድጋፍ ማግኘቷን አመልክተዋል።
በተለይም በመንገድ፣ በባቡርና በሀይል መሰረተ-ልማት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለመተሳሰር ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እንድታገኝ አስችሏል ብለዋል።
በመጪው የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ/ም የአፍሪካ ቀንድ የገንዘብ ሚኒስትሮችና አጋር አካላት በተገኙበት የኢኒሼቲቩ የፕሮጀክቶች አፈፃፀምና የአምስተኛ ዓመት ምስረታ መድረክ የሚካሄድ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ በዓለም ባንክ፣ በአውሮፓ ህብረትና በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረተ ቀጣናዊ የትብብር ማዕቀፍ ሲሆን ፥ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቩን ታስተባብራለች።