
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ25ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ዛሬ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በዕለቱ የመጀመሪያ መርሃ ግብር ቀን 9:30 አርሰናል ከሜዳው ውጭ ሌስተር ሲቲን የሚገጥምበት ጨዋታ ይጠበቃል።
በርካታ የፊት መስመር ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ያጡት መድፈኞቹ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።
ማንቸስተር ሲቲ በኢቲሃድ ኒውካስል ዩናይትድን የሚያስተናግድበት ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ አመሻሽ 12:00 ላይ ይደረጋል።
አስቶን ቪላ ከኢፕስዊች ታውን፣ ፉልሃም ከኖቲንግሃም ፎረስት፣ ሳውዛምፕተን ከቦርንመዝ፣ ዌስትሃም ከብሬንትፎርድ በተመሳሳይ 12:00 የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።
ክሪስታል ፓላስን ከኤቨርተን የሚያገናኘው የዛሬ የመጨረሻ መርሃ ግብር ምሽት 2:30 ሴልኸረስት ፓርክ ላይ የሚደረግ ይሆናል።
ትናንት ምሽት 5፡00 ላይ ብራይተን ቸልሲን በሜዳው ገጥሞ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።