የሶማሌና የአፋር ሕዝብ የወንድማማችነት መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሶማሌና የአፋር ክልሎች ሕዝብ የወንድማማችነት ግንኙነት ማጠናከሪያ መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ሃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።
ትናንት በተካሄደው የቅድመ ምክክር መድረክ የሰላም ሚኒስትር መሃመድ ኢድሪስ ተገኝተው እንደተናገሩት÷ የሶማሌና የአፋር ክልሎች ሕዝብ የጋራ ታሪክ ያላቸው፤ ለብዙ ዘመናትም በፍቅርና በአብሮነት የተሻገሩ ናቸው።
አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የወንድማማችነት መድረኩ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ መፍትሔ በመስጠት መግባባትንና የጋራ ልማትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።
የክልሎቹ ህዝቦች በጋራ የመልማት፣ የማደግና የመበልጸግ አቅም ያላቸው መሆናቸውን የሰላም ሚኒሰትሩ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረክ ላይ የሁለቱን ክልሎች ሕዝብ የወንድማማችነት ግንኙነት የሚያጠናክሩ የውይይት መነሻ ሃሳቦች ቀርበው ምክክር እንደሚደረግባቸው ተጠቁሟል፡፡