Fana: At a Speed of Life!

ቶዮ ሶላር ኩባንያ በኢትዮጵያ ያለውን ኢንቨስትመንት ወደ 110 ሚሊየን ዶላር ማድረሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኘው ቶዮ ሶላር ኩባንያ በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ወደ 110 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማድረሱ ተገልጿል።

ኩባንያው በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ በ60 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የተገነባውን ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ አጠናቅቆ ስራ ለማስጀመር እየመከረ ባለበት ወቅት ነው ይህንን የገለጸው፡፡

ኩባንያው ማስፋፊያ መደረጉን ተከትሎም በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ወደ 110 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማድረሱ ተመላክቷል፡፡

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጁንሴይ ሪዩ÷ ኩባንያው ለሶላር ሴል ምርቶች ያገኘው ዓለም አቀፋዊ ፍላጎት እና ትዕዛዝ ተጨማሪ ማስፋፊያዎችን እንዲያከናውን አድርጎታል ብለዋል፡፡

በ28 ሺህ ካሬ ሜትር ስኩዌር የሚደረገው የማስፋፊያ ስራ በፍጥነት እያደገ ላለው የኢትዮጵያ የታዳሽ ሃይል ኢንዱስትሪ ማዕከል የሚያግዝ ሲሆን÷ ግንባታውን በሐምሌ ወር በማጠናቀቅ የምርት ሂደቱን እስከ ነሐሴ ይጀምራል ተብሏል።

ኩባንያው በኅዳር ወር የተፈራረመው የ150 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሶላር አቅርቦት ስምምነት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ገበያ ላይ ወሳኝ ተዋናይ እንድትሆን ያስችላታልም መባሉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

የጃፓኑ የሶላር አምራች ኩባንያ የሆነው ቶዮ ሶላር በ47 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራዎችን ለማከናወን ማቀዱንም አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.