የትምህርት ዘርፉን ስብራቶች ለመጠገን የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል – ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ዘርፉን ስብራቶች በመጠገን ጥራትን ለማስጠበቅና መልካም ትውልድ ለመገንባት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ “ቅድሚያ ለትምህርት” በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት፥ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በትምህርት ዘርፉ የነበሩትን የቆዩ ችግሮች ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘርፉ ጥራት ለማስጠበቅና መልካም ትውልድ ለማፍራት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ የባለድርሻ አካላትና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሳ አደም በበኩላቸው፥ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመሩ ጥረቶችን ለማሳካት በትብብር መስራት ተገቢ መሆኑን ለማስገንዘብ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች፣ መምህራንና በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራሮችም መታደማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡