Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ለውጪ ገበያ ከቀረበ ማዕድን ከ604 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት ለውጪ ገበያ ከቀረበ ማዕድን 604 ሚሊየን 774 ሺህ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኦሮሚያ ክልል ማዕድን ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በክልሉ 76 የማዕድን ዓይነቶች መኖራቸውን ያነሱት የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዳዊት ለሜሳ፤ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወጪ ንግድን ማሳደግ፣ በብዛት እና በጥራት ማምረት፣ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪን ማበረታት እና የሥራ ዕድልን በመፍጠር የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የማዕድን ዘርፉ ግቦች መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

ለዚህም በዘርፉ የሚታዩ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር የማዕድን ልማት ስታንዳርድ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ መዋሉን ለፋና ዲጂታል አረጋግጠዋል፡፡

በዘርፉ የተከናወነውን ሪፎርም ተከትሎም ባለፉት የበጀት ዓመቱ ወራት ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረበ ማዕድን 1 ቢሊየን 640 ሚሊየን 182 ሺህ ብር መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ለ84 ሺህ 867 ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን እና ከውጪ የሚገቡ ማዕድናትን ለመተካት በተሠራ ሥራ 1 ሚሊየን 960 ሺህ ዶላር ማዳን መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በፀሐይ ጉሉማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.