Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቻይና የሁዋዌ ቴክ ፎር ጉድ ግሎባል ውድድርን አሸነፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ቴክ ፎር ጉድ ግሎባል ውድድርን አንደኛ በመሆን አሸንፈዋል።

ውድድሩ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በሚቆየውና በቻይና ቤጂንግ እና ሼንዘን የሚገኙ የቴክኖሎጂ ማዕከሎችን ጉብኝትና የተግባር ስልጠናዎችን ባካተተው ዝግጅት ነው የተካሄደው፡፡

በ6 ተማሪዎች የተወከለው የኢትዮጵያ ቡድን ተማሪዎቹን ከአዲስ አበባ፣ ሃሮማያ፣ ጅማ፣ ወልቂጤ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ማሰባሰቡ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ከሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አርጀንቲና፣ አየርላንድ፣ ማላዊ፣ ቬትናም፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና ሌሎችን ጨምሮ ከዓለም ዙሪያ ከተውጣጡ 12 ልዩ ቡድኖች ጋር መወዳደራቸው ተጠቁሟል፡፡

ተማሪዎቹ የእንስሳት ሕመሞችን አስቀድሞ ለመለየት በተዘጋጀውና በአርተፊሻል አስተውሎት በጎለበተው ኤርሊ ቬት በተሰኘው ፕሮጀክታቸው የተወዳደሩ ሲሆን÷በዚህም ትኩረት ለመሳብ መቻላቸው ነው የተገለጸው፡፡

ይህ የፈጠራ ፕሮጀክት ከተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች በተለይም ግብ 2 “ዜሮ ርሃብ” እና ግብ 15 “ህይወት በምድር” ከሚለው ጋር የተጣጣመ  ነው ተብሏል፡፡

በግብርና እና በእንስሳት ጤና ላይ ያሉ ወሳኝ ተግዳሮቶችን ይፈታል ተብሎ እንደሚታመን በውድድሩ መብራራቱንም የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የሁዋዌ ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስተር ሊሚንግ ዬ÷ ድሉ የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ልዩ ችሎታ እና ፈጠራ የታየበት ነው ብለዋል።

መጪው ትውልድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው የቴክኖሎጂ ገጽታ ውስጥ እንዲበለጽግ በሚያስፈልገውን ድጋፍ እና እድሎች ማመቻቸቱን ለማስቀጠል ሁዋዌ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.