4 ኪሎ ቤተ መንግስት ዙሪያ ያለው መንገድ ባለአንድ አቅጣጫ በመደረጉ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ፖሊስ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 4 ኪሎ ቤተ መንግስት ዙሪያ ባለ ሁለት አቅጣጫ የነበረው መንገድ ባለአንድ አቅጣጫ በመደረጉ አሽከርካሪዎች በደምብ መተላለፍ እንዳይቀጡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።
መንገዱ ባለአንድ አቅጣጫ እንዲሆን መደረጉን ባለማወቅ አንዳንድ አሽከርካሪዎች የተተከሉ የመንገድ ትራፊክ ምልክቶችን በመጣስ ለደምብ መተላለፍ ቅጣት እየተዳረጉ መሆናቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት፦
👉 ከጥይት ቤት መስቀለኛ እስከ ፓርላማ ትራፊክ መብራት ድረስ፣
👉 ከፓርላማ ትራፊክ መብራት እስከ ቅዱስ ገብርኤል (ሳይንስ ሙዚየም) ድረስ እንዲሁም
👉 ከቅዱስ ገብርኤል መስቀለኛ እስከ ጥይት ቤት ድረስ ቀድሞ የነበረው ባለ ሁለት አቅጣጫ መንገድ ወደ አንድ አቅጣጫ መንገድ መቀየራቸው ተገልጿል፡፡