በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበዓል ወቅት የምርት እጥረት እንዳያጋጥም ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበዓል ወቅት የምርት እጥረት እንዳያጋጥም በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ አስር ኢብራሂም መጪውን የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ አቅራቢ ነጋዴዎች የግብርና፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችን እና ሌሎች መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርቡና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጡ መግባባት ላይ መደረሱንም አመላክተዋል።
ሸማቹ በተለይም የቁም እንስሳት ግብይትን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በማድለብ ዘርፍ የሚገኙ አካላት ምርታቸውን ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ በአቋራጭ ለመበልፀግ ምርቶችን የሚደብቁ እና ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ማሳሰባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።