ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዓውድን በመገንዘብ እየተገኙ ያሉ ስኬቶችን ማስቀጠል ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዓውድን በመገንዘብ እየተገኙ ያሉ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ እና የዘርፎች ዕቅድ አፈጻጸም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት መገምገም ጀምሯል፡፡
በመድረኩ በ100 ቀናት የትኩረት ማዕከል የሆኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶች፣ የታዩ ክፍተቶች እና የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚታዩ ተመላክቷል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ እና በተለያዩ መስኮች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
በየዘርፉ የተሰሩ ሥራዎችን በአግባቡ መለካት፣ ማቅረብ እንዲሁም ለሌላው ማስረዳት እንደሚገባ ገልጸው÷ አሁንም አመራሩ በጊዜ የለኝም መንፈስ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ሰራተኛውን በአግባቡ የማይመራ፣ የማይመዝንና የማይከታተል መኖሩንና በጥቂት ታታሪ ሰራተኞችና ኃላፊዎች ተቋማት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ እንደሚስተዋል ገልጸው÷ይህንን መፈተሽ እና ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ባለፉት 9 ወራት ከታሰበው በላይ የተሳኩ ድሎች መመዝገባቸውን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ አሁንም ትኩረት የሚፈልጉ አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዓውድን በመገንዘብ እየተገኙ ያሉ ስኬቶችን ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰው÷ የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል ከዚህ በላይ መሮጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ እና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርምን መፈጸም ውዴታ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አገልግሎት አሰጣጥ ሁሉንም ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው÷በጠንካራ አመራር እና ሰራተኛ የታጀበ አገልግሎት አሰጣጥ መኖር እንዳለበት ነው ያስረዱት።
በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ከተገኙ ውጤቶች በላይ ለማሳካት ሁሉም በጊዜ የለኝም መንፈስ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።