Fana: At a Speed of Life!

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለወጪ ንግድ እድገት ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ለወጪ ንግድ እድገት ጉልህ ሚና ማበርከቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።

ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ በሀገሪቱ የንግድ ካባቢ ተወዳዳሪ መሆን የሚችልበትን አቅም የመፍጠር እና የተቀላጠፈ አሰራርን የመዘርጋት ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የንግድ ፈቃድና የዕድሳት አገልግሎት መሰጠቱንም አብራርተዋል።

ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ600 ሺህ ብልጫ ያለው መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በድህረ ፈቃድ ክትትልና ቁጥጥር 250 ሺህ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ እየተጠቀሙበት በመገኘታቸው ህጋዊ ርምጃ ተወስዶባቸዋል ነው ያሉት።

ባለፉት 9 ወራት የተመዘገበው የወጪ ንግድ ገቢ በታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ጠቁመው፥ ለዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትልቅ አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።

የምርት አቅርቦትንና ጥራትን በማሻሻል እንዲሁም የግብይት ተደራሽነትን በማስፋት የኑሮ ውድነትን ማረጋጋትና የንግዱን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ማሳደግ ላይ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

የገቢና ወጪ ምርቶች ላይ ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ አቅም 39 በመቶ እድገት እንዳሳየ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው ድርድር ግብ እንዲመታ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በቀጣይ ሦስት ወራት ወጪ ንግድን ማሳደግ፣ ዲጅታላይዜሽንን ማፋጠን፣ የኢ-ኮሜርስ ስራን ተቋማዊ ማድረግ፣ የጥራት ቁጥጥርን ማጠናከር እና የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣናን ወደ ሙከራ ትግበራ ማስገባት ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.