Fana: At a Speed of Life!

የኢኮኖሚ እድገቱን በቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳለጥ እየተሰራ ነው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ እድገት በቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

የ2017 በጀት ዓመት የ3ኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የ9 ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።

በዚህ ወቅት ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ÷ ለግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚውሉ የካፒታል እቃዎች ጨምሮ የገቢ ምርቶች በከፍተኛ መጠን ማደጋቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እየተገበረች በምትገኘው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ከፍተኛ ለውጥ ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኢኮኖሚ እድገቱን በትራንስፖርት ዘርፉ ለማሳለጥ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት፡፡

በዚህም ያለውን አቅም አሟጦ በመጠቀም በዘርፉ የአገልግሎት ቅልጥፍናን ማሳደግ መቻሉን ገልጸው÷የባቡር እና አሽከርካሪዎች የመፈጸም አቅም በማሳደግ በተከናወኑ ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን በማሳያነት አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በሎጂስቲክስ ዘርፍ እንዲሁም በወጪ እና ገቢ ንግድ ምርቶች ላይ ለተገኙ አመርቂ ስኬቶች ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።

የአፈር ማዳባሪያ ለአርሶ አደሩ በጊዜው ለማድረስ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷በዘንድሮው የምርት ዘመን እስከ አሁን 10 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን አመልክተዋል።

ይህም ከታቀደው 24 ሚሊየን ኩንታል አንጻር 42 በመቶ የሚሆነው ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙንና ቀሪውን በተሳካ ሁኔታ ለማምጣት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ዘርፍም በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ብቻ ሲከናወን የነበረውን ስራ ለ6 የግል ኩባንያዎች ፈቃድ በመስጠት የጭነትና የሎጂስቲክስ አቅምን ማሻሻል ተችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.