Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ልዑክ በአይ ኤም ኤፍ እና ዓለም ባንክ ስብሰባ ላይ ውጤታማ ውይይት አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንት አሚት ዳር በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) እና በዓለም ባንክ ስብሰባ ላይ ውጤታማ ውይይት አድርጓል።

ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ ታሪካዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር እና ኢትዮጵያ በቀጣይ የትብብር ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በድሃ ተኮር ማሻሻያዎች የተገኘውን ስኬት በተመለከተ አቶ አህመድ ሺዴ ገለጻ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያን የእድገት ስትራቴጂ በማክሮ ፋይናንሺያል ማገገም፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በኢነርጂ ደህንነት፣ በክልላዊ ንግድ እና ውህደት፣ በፋይናንስ ማካተት እና ሁለንተናዊ ብልፅግና ማስፈን ላይ ያተኮረ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል።

አሚት ዳር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ኢኮኖሚውን ለማዘመን የወሰደችውን የፖሊሲ ርምጃ አድንቀዋል።

የኢንቨስትመንት፣ የፖሊሲ ማሻሻያ፣ የግሉ ሴክተር ድጋፍ እና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጉዞ ወደ ሁሉን አቀፍ እድገትና ዘላቂ ልማት ለመውሰድ ባንኩ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።

ከስብሰባው ጎን ለጎን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከሳዑዲ የልማት ፈንድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሱልጣን አብዱልራህማን አል-ማርሻድ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።

ሱልጣን አብዱልራህማን አል-ማርሻድ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የፈጠረችውን ምቹ ሁኔታ እና ቀጣናዊ ትስስር እንዲጎለብት የምታደርገውን ጥረት አድንቀው፤ ተቋማቸው ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.