የአዲስ አበባ ከተማ የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷በግምገማ መድረኩ ያለፉት 9 ወራት ስኬታማ ስራዎችን በመፈተሽ ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ዝርዝር ግምገማ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ታቅደው ያልተፈፀሙና በ6 ወራት የሥራ ግምገማ ወቅት በዝርዝር ተለይተው በተሰጡ ግብረመልሶችና አቅጣጫዎች መሰረት የሕዝብ የቅሬታ ምንጭ የሆኑ ክፍተቶች አፈታት በጥልቀት ይገመገማልም ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም በመድረኩ የአመራሩ ችግር የመፍታት አቅም፣ የሚመራውን ተቋም ክፍተት በመለየት ምን ያህል ማሻሻል እንደቻለና ክፍተቶችን አስቀድሞ ለይቶ በፍጥነት መፍታት ላይ የመጡ ለውጦች እንደሚገመገሙ አመልክተዋል፡፡
በግምገማ መድረኩ የቀሪ ሶስት ወራት እቅዶችን በተሟላ ሁኔታ ለማሳካት የሚያስችሉ መግባባቶች ላይ እንደሚደረስ ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
የተለዩ ክፍተቶችን በማረም ለሕዝቡ በተገባው ቃል መሰረት ለማገልገል ራሳችንን ይበልጥ የምናዘጋጅበት ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡