ለደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ ቤተ-መንግስት የመልሶ ማልማት ሥራ ሊከናወን ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ ቤተ-መንግስት የጥገና እና የመልሶ ማልማት ሥራን ለማከናወን የውል ስምምነት መፈረሙን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ/ር) በዚህ ወቅት÷ የደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ ቤተ-መንግስት ጥንታዊና ታሪካዊ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ቤተ-መንግስቱ ለረጅም ዓመታት እድሳት ያልተደረገለት በመሆኑ በቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡
ቅርሱ ከጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተያያዙ ሥፍራዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከተመረጡት አንዱ መሆኑን ጠቁመው÷ የጥገናና የመልሶ ማልማት ሥራው የነበረውን አሻራና ይዘት በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን አሳስበዋል፡፡
የጥገና ሥራውን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ጥራቱን ጠብቆ በማከናወን ለሃገር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማድረግ ከቢዋይ ኤም ቲ ኮንትራክተር ጋር ስምምነት መፈረሙን ገልጸዋል፡፡
በነቀምቴ ከተማ የሚገኘው ቤተ-መንግስቱ በ1830 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን÷2 ነጥብ 5 ሄክታር የሚያካልል መሆኑንም የባለስልጣኑ መረጃ ያመላክታል፡፡