Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበልግ ወቅት አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በባስኬቶ ዞን ክልላዊ የበልግ ወቅት አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

“በአንድነት ችግኝን በመትከል የተራቆቱ አካባቢዎችን እናለማለን” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከናወነውን የበልግ ወቅት ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በይፋ አስጀምረውታል።

መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ችግኝን መትከልና ተፈጥሮን መጠበቅ፣ የተፈጥሮ አደጋን ለመቀነስ ብሎም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ አለው።

በክልሉ ሁሉም ዞኖች መርሀ ግብሩ እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ለመትከል ከታቀደው 198 ሚሊየን ችግኝ ውስጥ የቡና፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች መካተታቸውን ገልፀዋል።

በመርሀ ግብሩ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የባስኬቶ የላስካ ከተማ ነዋሪዎችና የላስካ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች መሳተፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.