Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ማነቃቃቱ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኮምቦልቻ ከተማ የኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃቱን እና ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን የከተማዋ ከንቲባ መሐመድ አሚን የሱፍ ገለጹ፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት ከንቲባው 127 ኢንዱስትሪዎች በማምረት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ኢንዱስትሪዎቹ 73 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ተኪ ምርት ማምረታቸውን እና ከ34 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በከተማዋ በግንባታ ላይ ለሚገኙት 110 ኢንዱስሪና ፋብሪካዎች ድጋፍ በማድረግ ወደ ምርት እንዲገቡና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የዘርፉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትም 11 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገዶችና ስድስት አማራጭ ድልድዮች እየተገነቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተፈሪ ታረቀኝ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ በዘርፉ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን ማቃለሉን አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም ሰፋፊ መሬት ለኢንቨስትመንት ማቅረብ መቻሉን፣ የቆሙ ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎቹ ወደ ምርት መግባታቸውን፣ በስፋት ተኪ ምርት መመረቱን እና የተሻለ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

በንቅናቄው የመሠረተ-ልማት ችግሮች መቃለላቸውን ጠቁመው፤ ምርታማነትን በማስፋት የክልሉን ኢኮኖሚ ማሳደግ መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡

በአለባቸው አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.