ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የደቡባዊ ዓለም ሀገራት ትብብር እንዲጠናከር ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡባዊ ዓለም ሀገራት ለጋራ ብልጽግና ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡
በብራዚል ሪዮ ዲ ጄኔሮ ሲካሄድ የቆየው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ተጠናቅቋል፡፡
ሚኒስትሩ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በዓለም የአሥተዳደር ሥርዓት እያጋጠሙ ያሉ ተገማች ያልሆኑ የፖለቲካ ቀውሶችን ጠቅሰው የደቡባዊ ዓለም ሀገራትን ትብብር መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
አካታች እና አሳታፊ በሆነ መንገድ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ሚናን ማጠናከር እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ሙሉ እና ውጤታማ ትግበራን ማረጋገጥ እንደሚገባም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
የደቡብ ደቡብን የጋራ ተጠቃሚነት ለማሳደግ፤ በግብርና፣ ኢነርጂ ልማት፣ ቴክኖሎጂ፣ አይ ሲ ቲ፣ ወታደራዊ እና በንግድ ግንኙነቶች ላይ መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡
ከሚኒስትሮች ውይይት ጎን ለጎንም ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸውም በኢኮኖሚና ንግድ ግንኙነቶች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ማጠናከር እንደሚገባ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡