አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጳዉሎስ ሆስፒታል ለጭፍራ ጤና ጣቢያ የመሠረታዊ የሕክምና መስጫ መሣሪያዎች እና መድሃኒቶችን አቀረበ።
ሆስፒታሉ ለጤና ጣቢያዉ በመጀመሪያ ዙር ድጋፉ፥ ለነፍጡር እናቶች እና ለወሊድ አገልግሎት የሚዉሉ መሣሪያዎች እና አልጋዎች ፣ የሰመመን ማሽን፣ የላብራቶሪ ማሽን ፣ መድሃኒቶች እና ሌሎች የሕክምና ግብዓቶችን አቅርቧል።
የጭፍራ ጤና ጣቢያው ከ19 ዓመታት በላይ ያደራጀውን የሕክምና መሣሪያ እና ቁሳቁስ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአካባቢው በወረራ በቆየበት ጊዜ ከፍተኛ ውድመት እና ስርቆት ፈጽሞበታል።
በመሆኑም ጤና ጣቢያዉን መልሶ ለማቋቋም እና አገልግሎቱን ከነበረዉ ላቅ አድርጎ ወደ ሆፒታል ለማሳደግ የጳውሎስ ሆስፒታል ሃላፊነቱን ወስዶ እየተንቀሳቀሰ እና የሕክምና ቁሶችንም ደረጀ በደረጃ በማሟላት ላይ መሆኑ ተመላክቷል።
ቀደም ሲልም የወደሙ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮችን እና ጀነሬተሮችን የማስጠገን ስራ በሆስፒታሉ ተከናዉኗል።
ጤና ጣቢያው ማዋለድን ጨምሮ የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና በከፊል የጀመረ ሲሆን፥ በሙሉ አቅም ለመጀመር የመሠረተ ልማቶችን መሟላት እየጠበቀ ይገኛል።
የጳዉሎስ ሆስፒታል ለጤና ጣቢያዉ የላከዉ መድሃኒቶች 784 ሺህ 900 ብር በላይ የሚገመት ሲሆን፥ የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎችና ግብዓቶች ደግሞ ከ1ሚሊየን 200 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸዉና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት አስቻይ መሆናቸዉን የጭፍራ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ሃላፊ አወል አሊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።
በፍሬህይወት ሰፊዉ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!