Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የተደራጀ ቡድን ድንገተኛ ተኩስ ከፍቶ የሕግ ታራሚዎች ማስመለጡንና ዝርፊያ መፈጸሙን የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጥር 30 ለየካቲት 1 አጥቢያ ሌሊት 7 ሰዓት ጀምሮ በላይ ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ በሚገኙ የወረዳ ማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ እና ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ላይ ጥቃት መድረሱን የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል።
ጉዳዩን አስመልክቶ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም በፋኖ ስም የሚነግድ የተደራጀ ቡድን ድንገተኛ ተኩስ ከፍቶ የሕግ ታራሚዎችን ማስመለጡን እና ከፍተኛ ዝርፊያ መፈጸሙ ተመላክቷል።
የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን መረጃው እንደደረሰው ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የጸጥታ ኀይሎች ስምሪት በመስጠት ጉዳዩን እየተከታተለ መሆኑን የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ውቤ ወንዴ ተናግረዋል።
የችግሩን መንስኤ እና ውጤት በማጣራት በአጥፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ፥ “ድርጊቱን የፈጸሙት ፋኖ ያልሆኑ ነገር ግን ፋኖ ነን የሚሉና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ናቸው” ብለዋል።
እነዚህ አካላት ታራሚዎች እንዲያመልጡ ማድረጋቸውን እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ እና በሚሊሻ ጽሕፈት ቤት የነበረን ትጥቅ ዘርፈው መውሰዳቸውን አመላክተዋል።
ኮሚሽኑ መረጃ እንደደረሰው ከዞኑ የጸጥታ አካላትና እና የፖለቲካ መሪዎች ጋር በመተባበር የኦፕሬሽን እና የወንጀል ምርመራ ቡድን በማሰማራት የተፈጸመውን ወንጀል የማጣራትና አጥፊዎችን የመቆጣጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም ያመለጡ ታራሚዎችን መልሶ በሕግ ቁጥጥር ስር የማዋልና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ከተዘረፈው የጦር መሳሪያ መካከል የተወሰነውን ማስመለስ እንደተቻለም አመላክተዋል።
የኦፕሬሽን እና የወንጀል ምርመራ ቡድኖቹ ቀሪ ሥራዎችን በትኩረት እየሠሩ ነውም ብለዋል።
በሂደቱ የዞኑ ሕዝብና የጸጥታ ኀይሉ ተቀናጅቶ አጥፊዎችን ለመቆጣጠር ርብርብ ማድረጉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በሌሎች አካባቢዎች መሰል ችግር እንዳይከሰት ሁሉም በንቃት አካባቢውን እንዲጠብቅም መልዕክት ማስተላለፋቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version