Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገርቱ በተለያዩ የጉምሩክ ኬላ ጣቢያዎች ላይ ግምታዊ ዋጋቸው ከ21 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ ከተያዙባቸው ቦታዎች መካካል መተማ፣ አዳማ፣ ባህር ዳር፣ ጅግጅጋ፣ ጋላፊ፣ ድሬደዋ፣ ሀረር፣ ሁመራ፣ ቦሌ አየር መንገድ፣ ሞጆ፣ አዋሽ እና ሌሎች የጉምሩክ ኬላ ጣቢያዎች ይገኙበታል።

ከተያዙት ህገ-ወጥ የገቢና ወጪ ዕቃዎች ውስጥም በሀሰተኛ ሠነድና በቱሪስት ስም የገቡ ተሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪዎች መለዋወጫ እቃ ይገኝበታል።

በተጨማሪም የአዋቂዎችና ህፃናት አልባሳት፣ ሲጋራ፣ የተለያየ ዓይነት የወርቅ መፈለጊያ ማሽንነሪዎች፣ ሁለት የትራክተር መሪ፣ 7 ሺህ 362 የመትረየስ፣ የክላሽና የቱርክ ሽጉጥ ጥይቶች እንዲሁም ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ በገቢ ዕቃ አወጣጥ ታክስ ሳይከፈል ሊጭበረበር የነበሩ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ናቸው የተያዙት።

ስራውን በቆራጥነት በመስራት ኮንትሮባንድስቶችን በማጋላጥ ህገ ወጥ ዕቃዎቹ ለሀገርና ህዝብ ገቢ እንዲሆን ላደረጉ ለጉምሩክ ሠራተኞቻችንና ተባባሪ አካላት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምስጋናውን አቅርቧል።

Exit mobile version