ጤና

ስለአዕምሮ ጤና ምን ያህል ያውቃሉ?

By Meseret Awoke

October 10, 2023

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዕምሮ ጤና ሰዎች ስለሚያስቡት፣ ስለሚሰማቸው እና በዚህም ስለሚያሳዩት ባህሪ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡

የአዕምሮ ጤና ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ሲሆን፥ ቀኑ ስለአዕምሮ ጤና ግንዛቤ በማስጨበጥና የተለያዩ መርሐ ግብሮችን በማከናወን በተለያዩ ሀገራት እየታሰበ ነው፡፡

የአእምሮ ጤና ሰዎች የህይወት ውጣውረድን ተቋቁመው እንዲኖሩ፣ ችሎታቸውን እንዲገነዘቡ፣ እንዲማሩና እንዲሰሩ እንዲሁም ለማህበረሰባቸው አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል የአእምሮ ደህንነት ነው።

ይህ የአዕምሮ ጤና ሲቃወስ ደግሞ የግለሰቡን የየዕለት ተግባር፣ ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት እና የሰውነት ሁኔታ ላይም ተጽዕኖ እንዳለው ይገለጻል፡፡

ዕድሜ፣ ጾታን፣ የገቢ ሁኔታን ወይም ዘር ሳይለይ ሁሉም ሰው ለአእምሮ ጤና መታወክ በሽታ የመጋለጥ ዕድል እንዳለው ሜዲካል ኒውስ ቱደይ በመረጃው ያስገነዝባል፡፡

ማህበራዊና የገቢ ሁኔታ፣ ጥሩ ያልሆኑ የልጅነት ልምዶች፣ አፈጣጠርና መሰረታዊ የጤና ሁኔታዎች የአንድን ሰው የአእምሮ ጤንነት ሊወስኑ እንደሚችሉም ነው የሚነገረው።

አብዛኛው የአእምሮ ጤና መታወክ ያለባቸው ሰዎች በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ የጤና ችግር እንደሚኖርባቸውም መረጃው አስነብቧል።

የአእምሮ ሕመም ዓይነቶች ጭንቀት፣ የስሜት መለዋወጥ (መቃወስ) እና ስኪዞፍሬኒያ (ከእውነታው ዓለም መዛባት) ናቸው፡፡

ጭንቀት፥ የተለመደ የአእምሮ ህመም ነው ይባላል፡፡ ይህ የአዕምሮ ጭንቀት ያጋጠማቸው ሰዎች ከአንዳንድ ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ ከፍተኛ ፍርሃት ወይም ጭንቀት አለባቸው።

የጭንቀት ምልክቶች ከሚባሉት ውስጥ እረፍት ማጣት፣ ድካም፣ ትኩረት አለማድረግ፣ የጡንቻ ህመምና የተቆራረጠ እንቅልፍ ይጠቀሳሉ፡፡

የስሜት መለዋወጥ(መቃወስ)፥ ከፍተኛ ደስታና ከፍተኛ ጭንቀት ሲፈራረቅ የሚስተዋል የአዕምሮ ህመም ዓይነት ነው፡፡

ድባቴ ከዚህ ቀደም ይዝናኑባቸው የነበሩት ተግባራት ላይ ፍላጎትን ሲያጡ ይታያል፡፡ ረዘም ላለ ጊዜም በሐዘን ድባብ ውስጥ ሊቆይ ይችላል ተብሏል፡፡

ባይፖላር ያለበት ሰው፥ በስሜት መዋዠቅና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ላይ ያልተለመደ ለውጥን ያስተናግዳል፡፡

ወቅታዊ ሁኔታን አማክሎ የሚከሰት የአዕምሮ መቃወስ፡- ከአየር ሁኔታዎች ጋር የተዛመደ የአዕምሮ ህመም ነው፡፡

ስኪዞፍሬኒያ (ከእውነታው ዓለም መዛባት)፡- ምንም ዓይነት የአካል ምርመራ የአእምሮ ሕመም እንዳለበት ላያሳይ ይችላል።

ይሁን እንጂ ሰዎች የአእምሮ ጤና መታወክ ሲያጋጥማቸው የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ፡-

• ከጓደኞች፣ ከቤተሰብና ከሥራ ባልደረቦች መራቅ፣ • በተለምዶ የሚወዷቸውን እንቅስቃሴዎች ማስወገድ፣ • በጣም ብዙ ወይም ትንሽ መተኛት፣ • በጣም ብዙ ወይም ትንሽ መመገብ፣ • የተስፋ መቁረጥ ስሜት፣ • አልኮል እና ኒኮቲንን ጨምሮ ስሜትን የሚቀይሩ ንጥረ ነገሮችን በብዛት መጠቀም፣ • አሉታዊ ስሜቶችን ማሳየት፣ • ግራ መጋባት፣ • እንደ ሥራ መሄድ ወይም ምግብ ማብሰል ያሉ የዕለት ተዕለት ተግባራቶችን አለመከወን፣ • በራሳቸው ወይም በሌሎች ላይ አካላዊ ጉዳት ለማድረስ ማሰብ እንዲሁም • ድምጽ በሌለበት ሁኔታ ድምጽ አለ ብሎ ማሰብ ይጠቀሳሉ፡፡

የአእምሮ ጤና ህመምን ለማከም የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይቻላል። ሆኖም ለአንዱ ሰው የሚሰራው የህክምና ዓይነት ለሌላው ላይሰራ ይችላል፡፡

በዚህም ሳይኮቴራፒ፣ ወይም የንግግር ሕክምና፣ መድሃኒትና ራስን ማከም(መንከባከብ) ለአዕምሮ ህክምና ከሚሰጡ ወይም መወሰድ ካለባቸው የህክምና ዓይነቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡