አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ንዴት ተፈጥሯዊ ስሜት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የሥነ-ልቦና ባለሙያው ሔኖክ ኃ/ማርያም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር የንዴት ስሜትን አስመልክተው ቆይታ አድርገዋል፡፡
የሥነ-ልቦና ባለሙያው እንደሚገልጹት የንዴት ስሜት መጥፎ ነው ወይም ጤናማ አይደለም የሚያስብለው አገላለጹ ነው፡፡
አንድ ሰው ንዴት ስሜት ውስጥ እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች ማወቅ ይቻላል ይላሉ።
በዚህም አካላዊ ለውጥ (የዓይን መቅላት፣ የደም ስር መገታተር፣ የልብ ምት መጨምር… ) በማሳየት ሰዎችን በማንጓጠጥ፣ በመሳደብ ሊገለጽ ይችላል፡፡
የንዴት ስሜትን መቆጣጠር ካልተቻለ የጤና፣ የሥነ ልቦና፣ የማህበራዊ ቀውስ እና አካላዊ ጉዳቶችን እንደሚያስከትልም ነው የሚናገሩት።፡
የማስተዋልና የፍቅር ስሜትን በማስወገድም ከራስና ከሰዎች ጋር የሚኖርን ግንኙነት እንዲሁም የማህበራዊ ህይወትን ያቃውሳልም ነው የሚሉት፡፡
የንዴት ዓይነቶች በሥነ ልቦና ውስጣዊና ውጫዊ በመባል ይከፈላሉ፡፡
የሥነ ልቦና ባለሙያው እንዳሉት ውስጣዊ የንዴት ስሜት በራስ ምክንያት የሚከሰት ሲሆን ፥ አደርጋለሁ ብለው የጠበቁትን ነገር ሳያደርጉ ሲቀሩ ወይንም ያሰቡት ሳይሆን ሲቀር የሚፈጠር ስሜት ነው፡፡
ውጫዊ የንዴት ስሜት ፥ በሰዎች ወይም አካባቢያዊ ጫናዎች ሲደርሱ የሚፈጠር ስሜት እንደሆነም ነው የሚገልጹት፡፡
ባህሪያቸው በፍጥነትና በድንገት የሚቀያየር ሰዎችና ችኩል ሰዎች በንዴት በቀላሉ የሚጠቁ ናቸውም ተብለዋል፡፡
ይህም ስሜት ብቸኝነት፣ ያለመፈለግ ስሜት፣ ድብርት፣ የበታችነት ስሜት፣ የማንነት ቀውስ ያስከትላል፣ ምርታማነትን ይቀንሳል፣ እርጅና ያፋጥናል፣ የልብና የደም ግፊት እንዲሁም የስኳር ሕመምን ያስከትላል፡፡
መፍትሄ • አየር ለጥቂት ደቂቃዎች ማስገባት ማስወጣት • ለመረጋጋት መሞከር • ዮጋ መስራት • መሰል ስሜቶችን ከሚያስከትሉ ሁኔታዎች መሸሽ