Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የእብድ ውሻ በሽታ ምንነት፣ምልክቶች እና መከላከያ መንገዶች

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የእብድ ውሻ በሽታ በቫይረሱ በተለከፉ እንስሳት ንክሻ ማለትም በውሻ፣ ቀበሮ፣ ተኩላና በሌሎች የሚመጣ እና ወደ ጤናማ ሰው ሊተላለፍ የሚችል አደገኛ በሽታ ነው፡፡

የእብድ ውሻ በሽታ በሌሊት ወፍ አማካኝነትም ሊተላለፍ የሚችል ሲሆን÷ በሽታው የሚከሰተው ራቢስ በተሰኘ ቫይረስ አማካኝነት ነው፡፡

በዚህ በሽታ የተያዘ እንስሳ የተለየ ጸባይ ማሳየት ይጀምራል፤ በተለይ የመቅበጥበጥና መበሳጨት ምልክት ያሳያል፤ አረፋ ይደፍቃል፣ መብላት ወይም መጠጣት አይችልም፣ አንዳንድ ጊዜ ያለምክንያት በመበርገግ ያገኘውን ሰው ወይም እንስሳ መንከስ እንዲሁም የለሃጭ መዝረብረብ ያሳያል፡፡

የቅድሚያ ምልክቶቹ ትኩሳት እና በተነከሱበት ቦታ ማሳከክ ወይም ማቃጠልን ያካትታል፤እነዚህ ምልክቶች ኃይል የታከለባቸው የሰውነት እንቅስቃሴዎች፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ መሸበር፣ የውኃ ፍራቻ፣ የሰውነት ክፍልን ለማንቀሳቀስ መቸገር፣ ግራ መጋባትና ህሊናን መሳት ምልክቶችን አስከትለው ይመጣሉ፡፡

ምልክቶቹ ከታዩ በኋላ የእብድ ውሻ በሽታ በአብዛኛው ሞትን ያስከትላል፤በዚህም በበሽታው የተያዘ እንስሳ ከ5 እስከ7 ባሉት ቀናት ውስጥ ለህልፈት ሊዳረግ የሚችልበት ሁኔታን ሊያጋጥም ይችላል፡፡

በሰዎች ላይ የሚታየው ምልክት ደግሞ ግለሰቡ ንቁ ቢሆንም ቁጡ ይሆናል፣ የብርሃን ጥላቻም ስለሚያድርበት ጨለማን ይመርጣል፣ በድንገት የመበርገግ ጸባይ ይታይበታል፤ በመጨረሻም አቅሉን ስቶ አረፋ እየደፈቀ ለሞት ይዳረጋል፡፡

የእብድ ውሻ በሽታ ወደ ሰዎች የሚተላለፈው በአበደ ውሻ ንክሻ ወይም በሌሎች በተለከፉ እንስሳት እንደመሆኑ በበሽታው የተበከለ እንስሳ ሌላ እንስሳ ወይም ሰው ሲቧጭር ወይም ሲናከስ የእብድ ውሻ በሽታ ሊያስተላለፍ ይችላል።

የተበከለ እንስሳ መራቅ ካልተቻለ ወይም የሰውነት ፈሳሽ አመንጭ ህዋስ ያሉበት ማስተላለፊያ ጋር ከተነካካ የእብድ ውሻ በሽታ ሊተላለፍ ይችላል።

አብዛኛዎቹ በሰዎች ላይ የተከሰቱ የእብድ ውሻ በሽታዎች መንስኤያቸው የውሻ ንክሻ መሆኑን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የበሽታው የመከላከያ መንገዶችም ከፍተኛ ተጋለጭነት ላለባቸው ሰዎች ለበሽታው ከመጋለጣቸው በፊት አስቀድሞ የመከላከያ ክትባትን መስጠት ይጠቀሳል፡፡

መወሰድ ያለበት ጥንቃቄም በአበደ ውሻ ወይም በሌላ ማንኛውም እንስሳ የተነከሰውን ወይም የተቧጨረውን ቦታ ለ15 ደቂቃ በውኃ እና በሳሙና ማጠብ፣ በአዮዲን ወይም በሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሾች ማጠብ ቫይረሱን ሊያስወግድ ይችላል፡፡

በተጨማሪም በሽታውን ለመከላከል ውሾችን በየጊዜው ማስከተብ፣ ከተነከስን ደግሞ በጤና ማዕከላት የሚሰጠውን ክትባትና ተያያዥ ሕክምና በጊዜ መውሰድ ይገባል፡፡

Exit mobile version