አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር አቀፍ የጤና አጠባበቅ ትምህርትና ተግባቦት ፎረም በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አማኑኤል ሀይሌ ÷ የጤና አጠባበቅ ትምህርትና ተግባቦት ስራ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ተላላፊ የሆኑ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የማህበረሰቡን የጤና ግንዛቤ ማሻሻል ላይ ተከታታይነት ያለው ትምህርት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡
በጤና ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ተገኔ ረጋሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ የጤና አጠባበቅ ትምህርትና ተግባቦት ስራ በተገቢው እንዲተገበርና የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስገኝ አደረጃጀቱን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ከጤና ሚኒስቴርና ሁሉም ክልሎች የተውጣጡ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላትና በዘርፉ የተሰማሩ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡