የሀገር ውስጥ ዜና

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመቄዶንያና ለጌርጌሴኖን ማዕከላት የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

By Alemayehu Geremew

January 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ሠራተኞቹ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እና ለጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃና ማገገሚያ ማዕከል የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።

አገልግሎቱ እና ሠራተኞች ያደረጉትን ከ500 ሺህ ብር በላይ እገዛ ያስረከቡት የተቋሙ ተወካይ፤ በተለያየ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁ ዜጎችን መደገፍ ከፍተኛ እርካታ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም አገልግሎቱ እንደዚህ አይነት ድጋፎችን በተደራጀ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

አገልግሎቱም ሠራተኞቹ አቅመ ደካሞችን፤ ረዳትና ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን በማስታወስ ለወገን ደራሽ ወገን በሚል ተነሳሽነት እገዛውን ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እና የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃና ማገገሚያ ማዕከል በተቋሙ ለተደረገው እገዛ ምስጋና አቅርበዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሕዝባዊ ተቋምነቱን እያስመሰከረ በመሆኑ እንደ ዜጋ ኩራት እንደሚሰማቸውም ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከዚህ ቀደም ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጀቶች እገዛ ሲያከናውን መቆየቱን ያስታወሰው የተቋሙ መረጃ፤ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል፡፡