Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የወላጆች የቁጣ ቃላት ልውውጥ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ጫና

አዲስ አበባ፣ የካቲት 04፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የልጆችን የቀጣይ ህይዎት መልክ ከማስያዝ አንጻር የወላጆች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

የስነ ልቦና ባለሙያ ዘላለም ይትባረክ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር የወላጆች የቁጣ ቃላት ልውውጥ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ጫና በሚል ሃሳብ ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም፥ ልጆች የሚማሩት ከንግግር ይልቅ በድርጊትና እና በማሳየት ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ቤተሰቦች የሚሉትን በመኖር ለልጆች አርዓያ እንዲሆኑ አደራ ያሉት የስነ ልቦና ባለሙያው፥ ግጭትንም ግጭት መፍታትንም ማሳየት እንደሚገባም ነው አክለው የተናገሩት፡፡

በልጆች ፊት ክፉ ነገር ሳይሆን የሚገነባ እና ጥሩ ስሜት የሚፈጥር ንግግር ማድረግ ለነገ ህይወታቸው የማይናቅ ሚናን እንደሚጫወት የስነ ልቦና ባለሙያው ዘላለም ይትባረክ ገልጸዋል፡፡

ጥሩ ያልሆኑ ቃላት የልጆች አዕምሮ ጤናማ በሆነ መንገድ እንዳያድግ ስለሚያደርግ ጥንቃቄ ይኑራችሁ ሲሉ ይመክራሉ፡፡

ችግር ሲፈጠር ይቅርታ መጠያየቅ፣ ችግሮችን በንግግር መፍታትና መመሰጋገን ባህል አድርጎ ማሳደግ ለልጆች የነገ ህይወት ጠቀሜታው ከፍ ያለ እና ችግሮችን በመነጋገር የሚፈቱ እንዲሆኑ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡

በዚህም የወላጆች የቁጣ ቃላት ልውውጥ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍ ያለ መሆኑን በመረዳት ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡና ተግባር ተኮር የሆነ ምክር እንዲሰጡ መክረዋል፡፡

Exit mobile version