የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ  እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች  የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው- ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

By Mikias Ayele

July 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ ፕሮጀክቶች  የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው  ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር)  ተናገሩ።

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡

በጉባኤው ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት÷በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር  ችግሮችን  ለመቅረፍ  የሚያስችሉ  የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በክልሉ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ  የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የሳኒቴሽን አገልግሎት ፣የድልድይ ፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በአጭር ጊዜ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የክልሉ የንጹህ መጠጥ  ውሃ ሽፋን 42 በመቶ መድረስ መቻሉን የገለፁት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመስኖ አውታሮችን ውጤታማና በዘላቂነት የሚያገለግሉ ለማድረግ በትኩረት  እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም  የድልድይ እና መንገድ ግንባታ አቅርቦትን በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤቶች  መመዝገባቸውን አንስተው በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ህዝቡ የልማቱ ተዋናይ መሆኑን ያሳየበት ነው ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡