የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል 354 የሕግ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ተባለ

By Shambel Mihret

July 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ ከ566 ሺህ በላይ ጉዳዮች እልባት ማግኘታቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለጸ፡፡

እየተካሄደ ባለው የሁለተኛ ቀን የጨፌ ኦሮሚያ 7ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2016 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀም እና የ2017 ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫዎች ሪፖርት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ጋዛሊ አባሲማል ቀርቧል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በሪፖርታቸው÷ በበጀት ዓመቱ ከ566 ሺህ በላይ ጉዳዮች እልባት ማግኘታቸውን በመግለጽ በፍትህ ዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተአማኒ ለማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

የስነ ምግባር ጉድለቶችን ማረም፣ የዲጂታል ፍትህ ስርዓት ማስፋፋት፣ ነፃ የህግ አገልግሎትና ጥብቅና አገልግሎት መስጠት እና የክልሉን የስራ ቋንቋ ለማያውቁ ዜጎች የትርጉም አገልግሎት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች የህብረተሰቡን ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከርና የፍትህ ስርዓትን በማገዝ ረገድ ካበረከቱት አስተዋፅኦ ጎን ለጎን የህዝቡን የቀደመ ዕሴት ያጎለበቱ መሆናቸውን ጋዛሊ አባሲማል ገልፀዋል።

በክልሉ በተቋቋሙ 6 ሺህ 505 የመጀመሪያ ደረጃ የባህል ፍርድ ቤቶች ከ40 ሺህ በላይ ጉዳዮች መፍትሄ ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በየደረጃው በተቋቋሙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ደግሞ ከ400 ሺህ 600 በላይ ጉዳዮች መፍትሄ መሰጠቱን ገልጸው በባህላዊ ፍርድ ቤቶች በተሰጡ ውሳኔዎች ባለጉዳዮች ያወጡት የነበረው ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የስነምግባር ጉድለትን ለመቀነስ ለ11 ሺህ 700 የህግ ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል ያሉት ጋዛሊ አባሲማል÷የስነ ምግባር ጉድለት በታየባቸው 354 የሕግ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

የፍትህ ዘርፉ እንዲሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

በመራኦል ከድር