Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኮሪደር ልማቱ በትብብር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው – የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት በትብብር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራር እና አባላት በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የኮሪድር ልማት ሥራ ተዘዋውረው ጎብኘተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ውብ ገጽታ የሚያላብስ ትልቅ ስራ ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ÷ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች እና የልማት ሥራዎች ላይ ከመንግስት ጋር በትብብር በመስራት ረገድ የተሻለ ቅርርብ እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ጉብኝቱ የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው÷ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ መሰል ልማቶች በሁሉም አካባቢዎች መስፋፋት እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ አባል መብራት ዓለሙ (ዶ/ር)  በበኩላቸው÷ “የኮሪደር ልማቱ እጅግ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው”  ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ምን ያህል በእድገት ጎዳና ላይ መሆኗን ሁነኛ ማሳያ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

በኮሪደር ልማቱ ከአካባቢያቸው የተነሱ ዜጎችም በመረጡት አግባብ ትክ መኖሪያ ቤት እንደተሰጣቸው መገንዘባቸውን ጠቅሰው÷ይህም ልማትን በዘላቂነት ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ መፎካከር እንጂ መሰል ልማቶችን መደገፍ ከሁሉም ፖለቲከኞች የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ወክለው በጉብኝቱ የተሳተፉት ብርሃኑ ጋዴቦ ናቸው፡፡

ይህም የዲሞክራሲ ባህል እንዲዳብር ወሳኝ ሚና አለው ነው ያሉት፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ልማቶች ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር በሚደረገው ስራ ላይ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ሌሎች የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የወለኔ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ወክለው በጉብኝቱ የተሳተፉት ፈይሰል አብዱላዚዝ ÷የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችን በጥራት እና ፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ የመጡት ፓስተር በየነ ደሳለኝ እና ከወለኔ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የመጡት መሃመድ ያሲን የኮሪደር ልማቱን እንደሚደግፉ ገልጸው÷መሰል ልማቶች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ እየተከናወነበት ያለው ፍጥነትና ጥራት  በትብብር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ከገዳ ስርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ የመጡት አባቦኩሩ ደበሌ÷ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ልማት ላይ ከመንግስት ጋር በጋራ መሰለፍ እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል፡፡

ከልማት ባሻገር መንግስት በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለመደገፍ በሚያደርገው ስራ ላይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አሻራ ማሳረፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

Exit mobile version