የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ሙስጠፌ  ህብረተሰቡ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቀረቡ

By Mikias Ayele

July 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ህብረተሰቡ የሚተከሉ ችግኞችን ጠቀሜታ በመገንዘብ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሶማሌ ክልል የክረምት ወቅት የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በዛሬው ዕለት በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።

አቶ ሙስጠፌ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷በክልሉ እየተተከሉ የሚገኙ ችግኞች ለህዝቡ ሕይወት፣ ለእንስሳቶች እና ለከተሞች ውበት የጎላ ጠቀሜታ አላቸው።

ህብረተሰቡ የሚተከሉ ችግኞችን ጠቀሜታ በመገንዘብ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በንቃት በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

በዕለቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ሌሎች አመራሮች በጅግጅጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

አመራሮቹ በኮሌጁ የተካሄዱ የማስዋብ እና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውንም የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡