የሀገር ውስጥ ዜና

የክልሉ መንግስት በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

By Shambel Mihret

July 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት በክልሉ ጎፋ ዞን በደረሰ የመሬት ናዳ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋምና ለመደገፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ቀበሌ በትናንትናው እለት በደረሰ ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኞች የተሰማቸውን ሀዘን በስፍራው ተገኝተዉ ገልጸዋል።

በአደጋው እስካሁን 229 ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ÷የሞቱ ሰዎች የአስክሬን ፍለጋ አሁንም ቀጥሏል ነው የተባለው፡፡

የክልሉ መንግስት በህይወት ለተረፉ ቤተሰቦች ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ ያለ ሲሆን ፥ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው የተነገረው።

የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ቦታዉ ድረስ በመሄድ የተሰማቸውን ሀዘን የገለጹ ሲሆን ፥ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች መጽናናትን ተመኝተዋል።

በቀጣይም የክልሉ መንግስት በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋምና ለመደገፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ከህዝቡ ጎን በመቆም የተጎዱትን ለመደገፍ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መግለጹን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በስፍራው ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡ ወገኖችን ካጽናኑት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ጸሐይ ወራሳ፣ የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባዉዲ፣ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አክሊሉ አዳኝ(ኢ/ር) ይገኙበታል፡፡