አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት ናዳ ለተጎዱ ዜጎች የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡
አደጋውን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽነው አገልግሎት ባወጣው የሀዘን መግለጫ÷ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በሰዎች ህይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብሏል።
መንግሥት ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትንና ብርታትን፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው በቶሎ ማገገምንም ተመኝቷል፡፡
መንግሥት የአደጋውን ተጎጂዎች ለመታደግ፣ በናዳ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ለማፈላለግና የነፍስ አድን ሥራዎችን ለማከናወን፣ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋምና የደረሰውን የጉዳት መጠን ለመለየት ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ አስቸኳይ የአደጋ መከላከል ግብረ ኃይል አቋቁሞ ወደ ስፍራው ልኳል ነው ያለው፡፡
መንግስት አስፈላጊውን የመልሶ ማቋቋም ሥራን ከአካባቢው የመንግሥት መዋቅር ጋር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡
የአደጋውን የጉዳት መጠንና የተጎጂዎች አጠቃላይ መረጃ በቀጣይ በተደራጀ አግባብ እንደሚገለፅ ተጠቁሟል፡፡