Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በክልሉ ሁለንተናዊ የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው-አቶ እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሁለንተናዊ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን  የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው ገለፁ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡

በጉባኤው ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት የ2016 የእቅድ ክንውን ሪፖርት÷  የማዕከላዊ ኢትዮጵያ በክልልነት ሲደራጅ ከህዝቡ ጋር ሰፊ ምክክር መደረጉን አንስተዋል፡፡

በዚህም ለዘመናት የቆዩ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን መፍታት ተችሏል  ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ÷እንዲሁም የክልሉ መንግስት በአደረጃጀት ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰከነ መንገድ እያየ እንደሚሔድም ተናግረዋል፡፡

የአመራር ስምሪትን እጅግ ሚዛናዊና የሁሉንም አካባቢ ውክልና ያረጋገጠ ሆኖ እንዲፈጸም ስለመደረጉም ገልፀዋል።

በሰላምና ጸጥታ፣በግብርና፣በስራ እድል ፈጠራ፣በገቢ፣የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት እና ሌሎችም ተግባራት የ100 ቀናት ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም የክልሉን የሰው ሀይል መዋቅር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ፈትሾ እንደገና ለማደራጀት የሚያስችል መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ ጥናት በመገባደድ ላይ እንደሚገኝ መግለፃቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version