አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ተፈጽሟል ከተባለ የንፁሃን ግድያ ጋር ተያይዞ ክስ የቀረበባቸው የክልሉ ፖሊስና የልዩ ኃይል አመራርና አባላት ከ14 እስከ 22 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ።
የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የህገ መንግስትና በህገ መንግስት ስርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።
ችሎቱ ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ በክሱ በተራ ቁጥር 1 የተከሰሱትን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከላቸውን ጠቅሶ በነጻ ማሰናበቱ ይታወሳል።
የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ክስ አቅርቦባቸው ከነበሩት በክስ መዝገቡ ከተጠቀሱ ተከሳሾች መካከል የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ፣ ም/ኮሚሽነር የነበሩት ቱት ኮር፣ የክልሉ የልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኮንግ ሬክ እና የክልሉ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡጀዲ ባሬን እና የተለያዩ የፀጥታ አባላቶችን ጨምሮ አጠቃላይ 15 ተከሳሾች ይገኙበታል።
ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ በጦርነት ጊዜ ንፁሃን ሰዎችን ለመጠበቅ ሲባል የወጣውን የጄኔቫ ቃል ስምምነት የፕሮቶኮል ድንጋጌን በመለተላለፍ እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/ንዑስ አንቀጽ 1 ሀ እና ለ፣ አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 270 ስር የተደነገጉ ድንጋጌዎችን መተላለፍ የሚል ነበር።
በዚህ በቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም የሸኔ ሽብር ቡድን እና የጋምቤላ ነጻ አውጪ ፓርቲ (ጋነግ) በጋራ በመሆን በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ 03 በኩል በፌደራል ፖሊስ ካምፕ እና በክልሉ ልዩ ኃይል እንዲሁም በሌሎች ፀጥታ አካላት ላይ የከፈቱትን ድንገተኛ ተኩስ ተከትሎ በወቅቱ በፀጥታ ኃይሎች የሽብር ቡድኑ ወደ መጣበት እንዲመለስ ከተደረገ በኋላ ማንነታቸው የተለዩ 35 ሰዎች እና ማንነታቸው ያልተለዩ ሌሎች ንፁሃን ዜጎች መረጃ ሰጥታችኋል በሚል ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ ትዕዛዝ በመስጠትና በግድያው የተሳተፉ አሉ በማለት የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሮ ነበር።
ተከሳሾቹ በዚህ መልኩ የተመሰረተባቸው ክስ ዝርዝር በችሎት እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት እንዳልፈጸሙ ጠቅሰው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ምስክሮች ቀርበው ይሰሙልኝ በማለት አጠቃላይ 37 ምስክሮች እንዳሉት ገልጾ የምስክር ቃል እንዲሰማለት ጠይቆ ነበር።
በፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ ካስመዘገባቸው ምስክሮች መካከል ከ15 በላይ የምስክሮችን ምስክርነት ቃል አዳምጧል።
በዚህ መልኩ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ ምስክር ቃል መርምሮ ከተከሳሾች መካከል የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ፣ ም/ኮሚሽነር የነበሩት ቱት ኮር እና የክልሉ የልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኮንግ ሬክ እና የክልሉ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡጀዲ ባሬን ጨምሮ 13 ተከሳሾች በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ተሰቶ ነበር፡፡
ሌሎች በዚሁ መዝገብ የተካተቱ 7ኛ እና 8ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ማለትም የጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል አባላት በነበረው በኮ/ል አቶሬ ጉር እና በጋምቤላ የፖሊስ ኮሚሽን አባል የነበረው ረ/ሳጅን ቾድ ቤንግ የተባሉ ተከሳሾችን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በቀረበባቸው ክስ ላይ በቂ ማስረጃ አለመሰማቱን ገልጾ በነጻ እንዲሰናበቱ ብይን መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ ያላቸውን ተከሳሾች በተለያዩ ቀናቶች በየደረጃው ያቀረቡትን የመከላከያ ማስረጃ መርምሯል።
በዚህም 12 ተከሳሾች የዐቃቤ ህግ ማስረጃን በበቂ ሁኔታ መከላከል አለመቻላቸው ተጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾችንና የዐቃቤ ህግን የቅጣት አስተያየት መርምሮ በመያዝ ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ ውሳኔ ሰጥቷል።
በዚህም 2ኛ ተከሳሽ የክልሉ የቀድሞ ም/ኮሚሽነር የነበሩት ቱት ኮር፣ 3ኛ ተከሳሽ የክልሉ የቀድሞ የልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኮንግ ሬክ እና 4ኛ ተከሳሽ የክልሉ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡጀዲ ባሬ እያንዳንዳቸው በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።
በተጨማሪም 6ኛ፣10ኛ፣ 11ኛ፣ 12ኛ እና 13ኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ16 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነ ሲሆን÷ 9ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ደግሞ በ15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።
ሌሎች በሌሉበት ጉዳያቸው የታየው 14ኛ እና 15ኛ ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው በ22 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።
በታሪክ አዱኛ