አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት 6 ቢሊየን 48 ሚሊዮን 494 ሺህ 966 ብር በጀት አጽድቋል፡፡
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡቦንግ ኡቶው ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የ2017 በጀት ዝርዝርና ክፍፍል የክልሉ በጀት ዋነኛ ምንጮች የክልሉ ታክስና ታክስ ያልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት የሚገኝ ድጎማ መሆኑን ገልጸዋል።
ለበጀት ዓመቱ እንዲውል ከተያዘው በጀት ውስጥ 2 ቢሊየን 973 ሚሊየን 68 ሺህ 17 ብር በክልሉ ከሚሰበሰብ ገቢ የሚሸፈን ሲሆን 3 ቢሊየን 75 ሚሊየን 426 ሺህ 949 ያህሉ ከፌደራል መንግሥት በድጎማ እንደሚሸፈን አብራርተዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ÷ በጀቱ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ባለው መንገድ ለታለመለት የልማት እቅድ ማስፈፀሚያነት መዋል እንዳለበት አሳስበዋል።
በመሆኑም የፀደቀው በጀት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡