Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢራን በከፍተኛ ቅዝቃዜና በኃይል እጥረት ሳቢያ ቢሮዎችና ት/ቤቶች ተዘጉ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢራን በርካታ ግዛቶች ውስጥ በተፈጠረ ከፍተኛ ቅዝቃዜ እና የኃይል እጥረት ምክንያት ቢሮዎችና ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ተሰምቷል፡፡

በአሜሪካ ኢነርጂ መረጃ አስተዳደር መሰረት ኢራን ግዙፍ የኃይል ምንጭ ያላት ሀገር ስትሆን በተፈጥሮ ጋዝ ክምችትም ከዓለም ሀገራት ሦስተኛ ደረጃን ትይዛለች።

ነገር ግን ሀገሪቱ ባለፉት ሳምንታት ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ እጥረት ገጥሟት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ እገዳ አስቀምጣለች።

ይህ የሆነው ከፍተኛውን ቅዝቃዜ ለመቋቋም ሲባል ዜጎች ለኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭነት ነዳጅ እየተጠቀሙ በመሆናቸው ነው ተብሏል።

ነገሮች ተባብሰው ዋና ከተማዋን ቴህራን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በቀዝቃዛው የአየር ጸባይ ምክንያት እና የነዳጅ ፍጆታን ለመቆጣጠር ሲባል ትምህርት ቤቶች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት መዘጋታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ከሰሞኑ ያልተጠበቀ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች እና በመዲናዋ ቴህራን በተደጋጋሚ ሲፈጠር መቆየቱን ዘገባው አካትቷል።

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ባሳለፍነው ሐሙስ ዕለት ዜጎቻቸው ኃይልን ለመቆጠብ ሲባል “ከሁለት ዲግሪ ያነሰ” ማሞቂያ እንዲጠቀሙ አሳስበው ነበር።

ኢራን በፈረንጆቹ 2022 በዓለም ሰባተኛዋ ድፍድፍ ዘይት አምራች ሀገር መሆን ችላ ነበር።

ቬንዙዌላ እና ሳዑዲ ዓረቢያን ተከትላ ሦስተኛዋ ትልቁ የተረጋገጠ የነዳጅ ክምችት ያላት ሀገር እንደሆነችም የአሜሪካ ኢነርጂ መረጃ አስተዳደር አስታውቋል።

ይሁን እንጂ በዘርፉ በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ባለመደረጉ እና በከፊል በምዕራባውያን ማዕቀብ ሳቢያ ሀገሪቱ ለሰሞነኛው የከፋ ችግር እንደተዳረገች ነው ዘገባው የሚያትተው።

Exit mobile version