ዓለምአቀፋዊ ዜና

ፕሬዚዳንት ፑቲን ከትራምፕ ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ

By Feven Bishaw

December 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።

 

ፑቲን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሊያገኘኝ ከፈለገ ዝግጁ ነኝ” በማለት ከትራምፕ ጋር ንግግር ካደረጉ አራት ዓመት እንደሆናቸው ተናግረዋል።

 

ሁለቱ መሪዎች ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የተገናኙት በፈረንጆቹ 2019 በጃፓን በተዘጋጀው የቡድን 20 ሀገራት ስብሰባ ወቅት ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት እንደነበርም የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል።

 

ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ ወዲህ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጋር ባለፈው መስከረም ወር በማራላጎ ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል።

 

ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ባደረጉት ንግግር ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ የሁለቱን ሀገራት ጦርነት በ24 ሰዓታት ውስጥ እንደሚያስቆሙ እንዲሁም ” የ2020ውን ምርጫ አሸንፌ ቢሆን ኖሮ ሁለቱ ሀገራት ጦርነት ውስጥ አይገቡም” ማለታቸውም የሚታወስ ነው።

 

ይሁን እንጂ ትራምፕ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ ከወር በላይ ቢቆጠርም የሁለቱን ሀገራት ጦርነት እንዴት ሊያስቆሙት እንዳሰቡ ያሉት ነገር የለም።