ስፓርት

የማንቼስትር ዩናይትድ ስታዲየም ኦልድትራፎርድ የአይጥ መንጋ አስቸግሮታል ተባለ

By yeshambel Mihert

December 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ዩናይትድ ሜዳ የሆነው ኦልድትራፎርድ በአይጥ መንጋ መቸገሩ ተሰምቷል፡፡

የንጽህና ተቆጣጣሪዎች በቅርቡ ባደረጉት ምልከታ÷ስታዲየሙ አይጥ በብዛት እንደመሸገበት መረዳታቸውንና ለቡድኑ የምግብ ንጽህና የሁለት ኮከብ ምዘና (ሬቲንግ) እንደሰጡት ተገልጿል።

በዚህም ለቡድኑ የምግብ ንጽህና ከአራት ኮከብ ወደ ሁለት ዝቅ ያለ ነጥብ እንደተሰጠውና የተፈጠረውን የጥራት መጓደል እንዲያሻሽል ምክረ ሃሳብ መቀበሉን ሜይል ኦንላይን ዘግቧል።

ተቆጣጣሪዎች ባደረጉት ፍተሻ በስታዲየሙ ምድር ላይ ባሉ ሱት በተባሉ ልዩ መዝናኛዎችና ኪዮስኮች ጭምር አይጥ እንደሚርመሰመስባቸው አረጋግጠዋል ተብሏል።

እግር ኳስ ቡድኑ አይጥንና ሌሎች ነፍሳትን ለመቆጣጠር ከጸረ-ተባይ ተቆጣጣሪ ድርጅቶች እና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ለዚህ ችግር የተጋለጠው ኦልድትራፎርድ በባቡር ሃዲድና በቦይ መካከል የተገነባ በመሆኑ ሳቢያ እንደሆነ በዘገባው ተጠቅሷል።

የማንቼስተር ዩናይትድ ቃል አቀባይ እንዳለው÷ በስታዲየሙ ሁሉም ክፍል ጠንከር ያለ የአይጥና ተባይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንና ምግብ በሚከማችበትና በሚዘጋጅበት ቦታ ሁሉ ከፍተኛ የንጽህና ጥንቃቄ ይወሰዳል።

ቡድኑ የተሰጠውን ደረጃ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ማንኛውንም አስፈላጊ የማሻሻያ እርምጃ እንደሚወስድ ነው ያረጋገጠው፡

በርካታዎቹ የፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ቡድኖች የ5 ኮከብ የምግብ ንጽህና ደረጃ እንዳላቸው የጠቀሰው ዘገባው÷ አዲሱ የቡድኑ ባለቤቶች ስታዲየሙን ለማደስ ካልሆነም እንደ አዲስ ለመስራት እያሰቡ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

በፈረንጆቹ 1910 የተገነባው ኦልድትራፎርድ እርጅናው ጸንቶበት ጣራው በተደጋጋሚ ሲያፈስ መታየቱ የተጠቆመ ሲሆን÷ ትናንት በቦርንማውዝ ከተሸነፈ በኋላ የቡድኑ አሰልጣኝ ለድህረ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ጣሪያው በማፍሰሱ ጋዜጠኞች ሲቸገሩ ታይተዋል።