ዓለምአቀፋዊ ዜና

እስራኤል በጋዛ ያካሄደችው ዘመቻ ለ6 ታጋቾች ሞት አስተዋጽዖ ማድረጉን አመነች

By ዮሐንስ ደርበው

December 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የእስራኤል ጦር በጋዛ ያካሄደው ዘመቻ ለ6 ታጋች እስራኤላዊያን በሃማስ መገደል አስተዋጽዖ ማድረጉን አስታወቀች።

ምንም እንኳን የምድር ጦሩ በጋዛ ጥንቃቄ የተሞላበት ዘመቻ ቢያካሂድም ባለፈው ነሐሴ ወር በሃማስ ለተገደሉት 6ቱ ታጋቾች ሞት አስተዋጽዖ ማድረጉ ተገልጿል።

የእስራኤል መንግስት አካሄድኩት ባለው ምርመራ ጦሩ ታጋቾቹ በራፋህ አካባቢ መኖራቸውን እንደማያውቅና ከጥቃት በኋላ የሟቾቹን አስከሬን ማግኘታቸውን አመልክቷል።

በወቅቱ የታጋቾቹ መገደል በእስራኤላዊያን ዘንድ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ቀስቅሶ ሰልፍ በመውጣት አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል።

የታጋቾችና የጠፉ ቤተሰቦች ፎረም የምርመራ ውጤቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በፈረንጆቹ ጥቅምት 7 የሃማስ ጥቃት ታጋቾችን በህይወት መመለስ የሚቻለው በድርድር ብቻ ነው የሚለውን አቋማችንን ያረጋገጠ ውጤት ነው ብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መንግስት ታጋቾችን ለማስለቀቅ በቂ ጥረት አላደረገም በሚል ከፍተኛ ተቃውሞና ትችት እየተሰነዘረበት መሆኑንም የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል።

ባለፈው ዓመት ሃማስ የእስራኤልን ድንበር ተሻግሮ ባደረሰው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 251 ሰዎች ደግሞ በቡድኑ ታግተው ተወስደዋል።

ከታገቱት ውስጥ 96 የሚሆኑት አስካሁን በሃማስ እጅ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመትና ቀሪዎቹ ደግሞ የእስራኤል ጦር ያስለቀቃቸው አንዲሁም አስከሬናቸው የተገኘባቸው መሆኑ ተመላክቷል።

በእስራኤል መንግስትና በሃማስ መካከል በሶስተኛ ወገን ተኩስ ለማቆምና ታጋቾችን ለማስለቀቅ ድርድሩ እንደቀጠለ ሲሆን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የድርድሩ ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል።