የሀገር ውስጥ ዜና

ጥምቀትን በጎንደር የባሕል ሳምንት ማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሄደ

By amele Demisew

January 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ሲካሄድ የነበረው ‘ጥምቀትን በጎንደር የባሕል ሳምንት’ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ጸጋየ በዚህ ወቅት÷ ከተማ አስተዳደሩ በዓሉን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጀት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በከተማዋ የተከናወኑ ልማቶች ለከተማዋ ውበት የፈጠሩ መሆናቸው ለበዓሉ ታዳሚዎች ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ለጥምቀት በዓል ለሚመጡ እንግዶች ጎንደር ጥቅል የመስህብ ቦታዎችን ማዘጋጀቷን ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ ቅርስ የአፄ ፋሲል አብያተ መንግሥት እድሳት መደረጉን እንዲሁም ደብረብርኃን ሥላሴ፣ ቁስቋምና ሌሎች መስህቦችም ዝግጁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ ምልከታ መካሄዱን ገልጸው÷ ሁሉም እንግዶቻቸውን በቀደመ እንግዳ ተቀባይ ባህል ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማን የጥምቀት በዓል አከባበርና ዝግጁነት አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፤ የጥምቀት በዓል ሰሞን ከሌላው ግዜ በተሻለ ኢንቨስተሮችን መሳብ የሚቻልበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል።

የጥምቀት በዓል ለጎንደር መታያዋና መድመቂያዋ ነው ያሉት ከንቲባው፤ ከሐይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትስስር የሚጠናከርበት እንዲሁም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ነው ብለዋል።

በሰላም አስመላሽ፣ ዓለምሰገድ አሳዬ እና ምናለ አየነው