Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ለከተራና ጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች የከተራና የጥምቀት በዓልን አስመልከቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ÷ ጥምቀት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ በዓል መሆኑን በመግለጽ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ÷ የጥምቀት በዓልን አስመልክተው ለመላው የእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ምዕመናኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብሩ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እና ትህትናን በመላበስ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው÷ ኃይማኖታዊ እሴቱንና ትውፊቱን ጠብቆ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፤ ከከተራው ጀምሮ አብሮነት፣ አንድነት፣ ፍቅር እና ትህትና የሚንፀባረቅበት ደማቅ በዓል መሆኑን በመግለጽ ለህዝበ ክርስቲያኑ እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የሀረሪ ክልላዊ መንግስት በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት÷ “በዓሉ በክልላችን ሲከበርም ሰላምንና አብሮነት በሚያጠናክር እና መከባበርንና መተሳሰብን በሚያጎለብት እንዲሁም ሀገራዊ ገፅታን በሚያሳድግ መልኩ ማክበር ይጠበቃል”ብሏል።

ህዝበ ክርስትያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖች በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት የተጠሙ ወገኖችን በማጠጣት እንዲሁም የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባም ገልጿል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ÷የከተራና የጥምቀት በዓላት ከሃይማኖታዊ ይዘታቸው ባሻገር የሀገርን ገጽታ ስለሚገነቡ ልንጠብቃቸውና ልናለማቸው ይገባል ያሉ ሲሆን፤ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻዉ ጣሰዉ(ዶ/ር) ÷ባስተላለፉት መልዕክት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ፤በዓሉን ስናከብር የብርታትና የተስፋ መንፈስ ተላብሰን ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ÷በዓሉን አብሮነትን በማጠናከር፣ ለሀገር ሠላም፣ ዕድገትና ብልጽግና በጋራ በመሥራት ማክበር እንደሚገባ በመጠቆም ፤ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ ለብርሃነ ጥምቀቱ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

በተመሳሳይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ÷ በዓሉን የተቸገሩትን በማሰብና የአብሮነት ዕሴቶቻችንን በማጉላት ማክበር ይገባል ብለዋል፡፡

ይህም የበዓሉን ተፈጥሮአዊ ዓላማውን ከማሳካት ባለፈ የእርስ በርስ ግንኙነታችንን እንዲሁም አብሮነታችንና አንድነታችንን የሚያጎለብት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መተሳሰብ አብሮነትና ጠንካራ አንድነት ለዘላቂ ሰላምና ልማት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ የበዓሉን አስተዋጽኦ መጠቀም ይገባናል ስሉም አስገንዝበዋል፡፡

እንዲሁም የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ክብረ በዓሉ የእውነተኛ ኅብረ-ብሔራዊነት ማሳያ፣ የወንድማማችነት እና እህትማማችነት መገለጫ እና የአብሮነታችን ሰበዝ ነው ብለዋል፡፡

በዓሉ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የፍቅርና የሰላም እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version