አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ጋምቤላ ከተማ ናት፡፡
በባሮ ወንዝ ላይ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በጋምቤላና አካባቢው በሚገኙ የክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድ በናፍቆት የሚጠበቅ ልዩ ድባብ ያለው ትልቅ ሐይማኖታዊ በዓል ነው፡፡
የከተራና የጥምቀት በዓላት በጋምቤላ ባሮ ወንዝ ላይ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ ለሥድስት ቀናት በድምቀት መከበሩ ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡
በከተራ ዕለት በከተማዋ የሚገኙ 44 ታቦታት ወደ ባሮ ወንዝ ይወርዳሉ፤ ከጥምቀት ቀን ጀምሮ ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናትም ታቦታቱ ወደ አድባራቸው ይገባሉ፡፡
በጥምቀት ዕለትም ጠዋት ላይ በርካታ ምዕመናን በባሮ ወንዝ በመገኘት ፀበል ይረጫሉ፡፡
ቆየት ብለውም የቅዱስ ገብርኤልን እና የኪዳነ ምኅረትን ጨምሮ ሌሎች ታቦታትን ይሸኛ፤ ሌሎች ሐይማኖታዊ ሥርዓቶችንም ይከውናሉ፡፡
ከሽኝት መርሐ-ግብሩ በኋላም ምዕመናኑ በባሮ ወንዝ ዙሪያ በሚካሄደው የማታ ጉባዔ ላይ በዝማሬና ምሥጋና ያደምቃል፡፡
በጋምቤላ ከሚገኙ ብሔረሰቦች በተጨማሪ በበዓሉ ላይ ለመታደም ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ እንግዶች እና የውጪ ሀገር ዜጎች መበራከት ደግሞ በዓሉን ይበልጥ ያደምቀዋል፡፡