Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሁቲ አማጺያን በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ትዕዛዝ ሰጡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በየመን የሚገኙት የሁቲ አማጺያን በድጋሚ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በሰሜናዊ የመን የሚንቀሳቀሱት የሁቲ አማጺያን በውጭ የሽብር ቡድን መዝገብ ውስጥ እንዲካተቱ በሚያዘው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ መፈረማቸው ተገልጿል፡፡

አማጺያኑ በመጀመሪያ ዙር የትራምፕ አስተዳደር በሽብር ቡድን መዝገብ ውስጥ ተካትተው የነበረ ሲሆን÷ በ2021 ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በየመን የሚደረገውን ሰብዓዊ እርዳታ ለማሳለጥ በሚል ቡድኑን ከሽብር መዝገብ መሰረዛቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ከቀናት በፊት ወደ ቀድሞ መንበራቸው የተመለሱት ፕሬዚዳንት ትራምፕ አማጺያኑ በሽብርተኝነት መዝገብ ውስጥ እንዲካተቱ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አል አረቢያ ዘግቧል፡፡

የሁቲ አማጺያን ወይም አንሳር አላህ በመባል የሚታወቀው የፖለቲካና ወታደራዊ ክንፍ የየመንን ማዕከላዊ መንግስት በመቃወም በ1990ዎቹ የተመሰረተ ሲሆን÷ በየመን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተሳትፎ እንደነበረው ይነገራል፡፡

በቀድሞ የሂዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ ስልጠና እንደወሰዱ በሚነገርላቸው የየመኑ ፖለቲካኛ አብዱል ማሊክ አል ሁቲ የተመሰረቱት አማጺያኑ የሁቲ ነገድ ወይም ዛይዲ ሺዓ ሙስሊሞች መሆናቸው በዘገባው ተመላክቷል፡፡

ኢራን በቀጣናው ያላትን አላማ ለማሳካት ስልት አማጺያኑን በገንዘብ እና በጦር መሳሪያ ለበርካታ ዓመታት ስትደግፍ መቆየቷ ተጠቁሟል፡፡

አማጺያኑ ሃማስ እስራኤልን ካጠቃበት ጊዜ ጀምሮ ለጋዛ ድጋፋቸውን ለመግለጽ  አሜሪካ እና እስራኤል ጋር ግንኙነት ባላቸው መርከቦች  ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version