የሀገር ውስጥ ዜና

6 ሺህ የልብ ህሙማን የቀዶ ህክምና ወረፋ ላይ ናቸው

By amele Demisew

January 25, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጤና ሚኒስቴር ከክልልና ከተማ አስተዳድር ጤና ቢሮዎች ጋር የቀዶ ህክምና ወረፋን ለማስቀረት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

4ኛው ምዕራፍ የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት የግማሽ ዓመት አፈጻጸም መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል ።

ጥምረቱ የጤና ተቋማት ልምድ የሚለዋወጡበት፣ግብዓት የሚዋዋሱበት፣የሚደጋገፉበት መሆኑንና ሃብትን በመቆጠብ በጤና አገልግሎት ስርዓቱ ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል ።

በጤናው ዘርፍ ላይ ያሉ አገልግሎቶች በየጊዜው መሻሻል እየታየባቸው ቢሆንም አሁንም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን አንስተዋል።

በተለይ አሁን ላይ እንደ ሀገር ከፍተኛ የሆነ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ፈላጊ ክምችት መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ክምችት በዚህ ዓመት መጠናቀቅ እንዳለበትም ሚኒስትሯ አቅጣጫ አስቀምጠዋል ።

በዛሬው ዕለትም ሚኒስትሯ ይህንን ክምችት ማቃለል የሚያስችል ስምምነት ከሁሉም ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የጤና ቢሮ ተወካዮች ጋር ተፈራርመዋል።

አሁን ላይ በሀገሪቱ 6ሺህ ሰዎች የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወረፋ እየጠበቁ ሲሆን÷ ይህንን ችግር ለመፍታት መንግስት ከአጋር አካላት ጋር በርብርብ እየሰራ ነው ብለዋል ።

በሌላ በኩል ሚኒስትሯ የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት አባል የሆኑ የጤና ተቋማት ፤የአገልግሎት ጥራት ማምጣት ፣የጽዱ ጤና ተቋም መፍጠር እንዲሁም የደም አቅርቦት ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል ።

በመሳፍንት እያዩ