አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሰባት አመታት ተቋርጦ የነበረው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስፖርት ፌስቲቫል ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ(ፕ/ር) ÷የስፖርት ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱ ጥቅሙ የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአምስት የስፖርት አይነት ከ 49 የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተማሪዎች የሚሳተፉበት ይህ ውድድር ተማሪዎችን እርስ በርስ የሚያስተሳስር እና የሚያቀራርብ እንደሆነ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ መክዩ መሃመድ ተናግረዋል።
ደማቅ በነበረው የመክፈቻ ስነ -ስርዓት ተማሪዎችም የመጡበት አካባቢ የሚወክል ባህላዊ ትርዒት አሳይተዋል።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ ውድድር ጥር 27 ቀን 2017ዓ.ም ፍፃሜውን ያገኛል።
በዳዊት መሃሪ